ኢኢቢ: ጥር 14/2017 ዓ.ም (ባህርዳር) በታሪክ፣ በባሕል፣ በቅርስ፣ በትምህርት እና በሃይማኖት ጥንታዊ ከሚባሉት የሀገራችን ከተሞች መካከል ጎንደር ቅድሚያ ተጠቃሽ ናት።
ጎንደር ስትነሳ መስራቿ አጼ ፋሲለደስ ትተውት ባለፉት አሻራ አብረው ቢታወሱም ስሟ ቀደም ብሎም በአጼ አምደጽዮን ዜና መዋዕል መጠቀሱ የጎንደርን የምሥረታ ዘመን ከማስላት ጥንታዊት ብሎ ማለፍ ሳይቀል አይቀርም ይባላል። ይች ጥንታዊ እና ታሪካዊት ከተማ ስሟ ከሥልጣኔ፣ ከንግድ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከኪነ ጥበብ እና ኪነ ሕንጻ ጋር በእጅጉ ተቆራኝቶ ይጠራል።
ጎንደር የምትገኝበት መልካምድራዊ አቀማመጥ እና ከጎረቤት ሀገራት ድንበር በቅርብ እርቀት ላይ መክተሟ ለውጭ ንግድ እና ለኢንቨስትመንት ዐይነ ግቡ ከተማ ያደርጋታል።
ከዘመናት በኋላ በተለይም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የጎንደር የንግድ ልውውጥ መቀዛቀዝ ብቻ ሳይኾን የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መዳከም በእጅጉ ተስተውሎባታል። ያንን የዓመታት ቁጭት እና የዘመናት ክፍተት ለመሙላት እና ወደቀደመ ገናናነቷ ለመመለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” የኢግዚቢሽን እና ውይይት መድረክ በጎንደር ተካሂዷል።
በኢግዚቢሽን እና የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በየጊዜው ብዙ ዕድሎች ወደኛ ይመጣሉ ነገር ግን ሳንጠቀምባቸው ይባክናሉ ብለዋል። ይህን ታሪክ ለመቀየር የሚያስችል መግባባት እየተፈጠረ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ጎንደር እና አካባቢውን ለማልማት እና ለመለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ፀጋዎች አሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ደረጃ በደረጃ እየለዩ እና እየተጠቀሙ ለመለወጥ የሕዝብ እና መንግሥት መግባባትን ይጠይቃል ነው ያሉት። አሁን ላይ የከፍታውን ዘመን ለመመለስ የሚያስችል መደማመጥ፣ መቀራረብ እና መነጋገር እየተፈጠረ ነው ብለዋል። የያዝነው መንገድ የትናንት ታሪክን የምንዘክርበት ብቻ ሳይኾን ዛሬም አዲስ ታሪክ የምንሠራበት ነው ብለዋል።
በክልሉ ካሉ ስድስት ልዩ የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ቀጣናዎች አንጻር የተሳሰረ ጥናት እየተደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዩሐንስ አማረ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን አይቶ እና ለይቶ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጋር አካላት፣ አበዳሪ ተቋማት፣ የመሠረተ ልማት ተቋማት እና የክልሉ የኢንቨስትመንት ቦርድ አልሚ ባለሀብቶች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በፍጥነት እንዲፈቱ መሰል የውይይት መድረኮች እንደሚያስፈልጉም ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥት እና የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ በአልሚ ባለሀብቶች የሚቀርቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ለመፍታት እየሠራ እንደኾነም አንስተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ የአንድ መስኮት አገልግሎት ደንብ ፀድቆ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተግባራዊ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች አንዷ ጎንደር መኾኗንም ጠቁመዋል።
ከዞን የሚመጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት መርምሮ መወሰን እና መሠረተ ልማት ማሟላት የቦርዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል። ኢንቨስትመንት በባህሪው ሰላም ይፈልጋል ያሉት አቶ ዩሐንስ ባለሀብቱ እና ሕዝቡ ሰላሙን ሊያስጠብቅ እንደሚገባም አስረድተዋል። አሚኮ




See insights and ads
All reactions:
21ሞላ ደሱ መኮነን and 20 others