ስለ አማራ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

                     የቢሮው አመሰራረት

መጀመሪያ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ስም በመቀጠል ደግሞ በንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ስር ተዋቅሮ የነበረው የኢንዱስትሪ ዘርፍ የመጨረሻ ግባቸው ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የክልሉን ህዝቦች የልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል ሆኖ እያለ በተለያየ ተቋም ስር በመደራጀታቸው አቅማቸው ከመበታተኑም በላይ በተግባርና ኃላፊነት መደራረብ  ምክንያት ከአላስፈላጊ የጉልብትና ገንዘብ ብክነት በተጨማሪ አልፎ አልፎም ቢሆን በመገፋፋት  ውጤታማ ስራ ሳይሰሩ ቆይተዋል፡፡ ስለሆነም ይህን ችግር በውል የተገነዘበው የአማራ ክልል ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 264/2011 አንቀጽ 10 እንደተደነገገው በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ  ስር የነበረውን የኢንዱስትሪ ዘርፍና ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን በአንድ በማዋሃድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮን አቋቁሟል፡፡

ቢሮው የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር ለመፈፀም ከዚህ ቀደም በ10 ዞኖቸን በ3 ሜትሮፖሊታን ከተማ አስተዳደሮች ብቻ የነበረውን አደረጃጀት በአዲሱ መዋቅር በ14 ዞኖች፤ በ8 ሪጅኦፖሊታን ከተሞች እና አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤትን ጨምሮ እንዲሁም በውስጣቸው ባሉ 162 ከተማና የገጠር ወረዳዎች በጽ/ቤት ደረጃ አደረጃጀት ዘርግቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ ኢንቨስትመንት ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከፍቶ በተለይ ከውጭ ለሚመጡ ባለሃብቶች በቅርበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከቢሮው ጋር በቀጥታ ተዛማጅነት ያላቸው ተግባራት የሚያከናውኑ የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ለቢሮው ተጠሪ ተቋም እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ተቋሙም የሚመራባቸው አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እንዲሁም ሌሎች የአሰራር ሰርዓቶች ተዘርግተው ግልፅነትን የሚፈጥሩ፣ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ሁነው ተዘጋጅተዋል፡፡

የአብክመ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

ቢሮው የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በባለቤትነት የመምራትና የማስተባበር ተልዕኮውን ለመወጣት እንዲችል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በቀጣዮቹ ዓመታትም በዋነኝነት  ሰፊ የሰው ሀይል፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት በስፋት በሚጠቀሙ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉ፣ ወጪ ምርቶችን በስፋት የሚልኩ እና የገቢ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በማተኮር የሚሰራ ነው፡፡

ክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ክልሉን ብሎም ሃገርን ሊለውጡ የሚችሉ የተለያዩ አይነት ፀጋዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ አካባቢ ያለውን ሀብት መሰረት አድርጎ በየትኛው ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለብን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ የትኩረት ዘርፎችንና አካባቢዎችን/ቦታዎችን በ6 ዋና ዋና ቀጠናዎች ማለትም ተከዜ ተፋሰስ፤ሰሜን ምዕራብ አማራ፤ደቡብ ምዕራብ አማራ፤የአባይ ሸለቆ፤ምስራቅ አማራ እና የጣና መቀነት በሚል የለየ አንድ የክልሉ ኢንዱሰትሪና ኢንቨስትምንት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪ በተለዩ ቀጠናዎች ውስጥ ከአሁን በፊት የአዋጭነት ጥናት የተሰራላቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወቅታዊ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

Scroll to Top