“ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በባሕርዳር እምርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ የሚያስችል ንቅናቄ መጀመሩን የባሕርዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

****************************************

ኢኢቢ፡ ታህሳስ 17/2017 ባሕርዳር)

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሀሳብ የስትሪንግ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን በዚህም የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ፣የከተማው ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን ፣በም/ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃን ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች አጋርና ባለድርሻዎች በተገኙበት አካሂዷል።

በም/ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃን ንጉሴ በንቅናቄ መድረኩ ለተገኙ አጋርና ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች እንደገለፁት ካለፈው ዓመት የቀጠለ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደ ሀገር እየተከናወነ መሆኑን በማንሳት ባሕርዳር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በህዝባችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለቸውን ምርቶች በማቅረብ የሚታወቁ የትልልቅና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ያን ሊመጥን የሚችል ምርትና ምርታማነት በመፍጠር በኩል ገና ያልተደረሰባቸው ጉልህ ስራዎች ከፊት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ስለሆነም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳብ አመንጭነት እየተካሄደ ያለው “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” አገራዊ ንቅናቄ ለከተማችን ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አበርክቶ ስላለው ከተለያዩ አጋርና ባለድርሻ ተቋማት የተወጣጣው ስትሪንግ ኮሜቴ መላ ማህበረሰቡን ፣ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እና ሌሎች ለስራው ውጤታማነት አጋዥ የሆኑ አካላትን በማነቃነቅ ካለፈው ዓመት በተሻለ በመፈፀም የከተማችንን ለውጥ አንድ እርምጃ ወደፊት በማስቀጠል የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ጭምር ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል የሚሉና መሰል መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በንቅናቄ መድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳቦች የማጠቃለያ ማብራሪያና የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን መንግስት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት በርካታ የተግባር ስልቶችን በመንደፍ ከፍተኛ ትግል እያደረገ መሆኑንና “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄም ዋነኛው የለውጥ ማረጋገጫ ድርጊት መሆኑ ተረጋግጦ ከፌደራል እስከ ታች ክልልና ከተሞች ድረስ በትኩረት እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ይህም ንቅናቄ መላ ህዝባችንን ጨምሮ የአጋርና ባለድርሻ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ ፣ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች በጥናትና ምርምር ሊያጠናክሩት የሚገባ ፣በኢንዱስትሪ የበለፀገ ማህበረሰብ መፍጠር የሚያስችል ፣አገር በቀል ምርቶችን በስፋት እያመረቱ በማሳደግ የፍጆታ ምርት እጥረትን ከመቀነስ ባለፈ የውጭ ምንዛሬን ማምጣት እንዲሁም ሞዴል የሆነ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለውቧ ባሕርዳር መገለጫዋ እንዲሆን መስራትን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄን ካለፈው በጀት ዓመት በተሻለ አቅም ለማከናወን አምራች ኢንዱስትሪውን ለስኬታማ ስራ ከማነቃቃት ጀምሮ የሚከናወኑ አጠቃላይ ተግባራትን በውጤታማነት በመፈፀም ስማርት ባሕርዳርን በምርትና ምርታማነት እድገት የምትገለፅ ከተማ እንድትሆን ባልተቆራረጠ ቅንጅታዊ የስራ መርህ ታግዞ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top