ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 38 ባለሃብቶች ፈቃድ መስጠታቸውን የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ ።

*****************************************************

ኢኢቢ: ታህሳስ 17/2017 ዓ.ም. ፡ባህርዳር

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ወንዴ እንደገለፁት በየደረጃው የሚገኙት የኢንቨስትመንት ተቋማት በየአካባቢው ኢንቨስተሮች በሚፈልጉት ልማት ዘርፎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ፣ መደገፍና በስራቸው ላይ እንቅፋት ሲያጋጥም መፍትሔ ማፈላለግ ዋነኛ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ፈቃዱ አያይዘውም በብሄረሰብ አስተዳደሩ 1 ነጥብ 484 ቢሊየን ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ኢንቨስተሮች ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው 38 ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ከ6 ሺህ 200 በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ገልፀዋል።

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በሁሉም ኢንቨስትመንት ዘርፎች ምቹ፣ ትርፍ አምራች ፣ የግብአት እጥረት የሌለበትና ተዝቆ የማያልቅ የተከማቸ ማዕድን የሚገኝበት ዞን መሆኑን የጠቀሱት መምሪያ ኃላፊ ለሆቴልና ቱሪዝም ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከሶስተኛ ወገን ነፃ የሆነ መሬት መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንዳይገቡ ስጋት መፍጠር ፣ ንብረታቸው ላይ ጉዳት ማድረስና የገበያ ትስስር መላላት የፀጥታ ችግር የፈጠረባቸው እንቅፋቶች መሆኑን የገለፁት አቶ ፈቃዱ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ፣ መሬት ከሶስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ አለመስጠትና የፋይናንስ ድጋፍ ውስን መሆን ተጨማሪ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንት ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን በመረዳት በየደረጃው የሚገኙት የኢንቨስትመንት ተቋማት ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ከ3ኛ ወገን ነፃ የሆነ መሬት በማቅረብና ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባቸው የጠቀሱት አቶ ፈቃዱ ብሄረሰብ አስተዳደሩ በሁሉም ለኢንቨስትመንት ዘርፎች ምቹና ትርፋማ የሚሆኑበት አካባቢ በመሆኑ በሚፈልጉት ዘርፍ ተሰማርተው እራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ጥሪ አስተላልፈዋል። አዊ ኮሚኒኬሽን እንደዘገበው

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top