የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የውጭ ንግድ እና ተኪ ምርትን ለማሳደግ ያለመ ምክክር ከአጋሮቹ ጋር በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ንግድ አና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) መርሐ ግብሩ በዋናነት በግብርና ዘርፍ የተገኙ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ሂደት ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በቂ ግብዓት ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት መጠበቅ ቢሮው ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል እንደኾኑ ጠቁመዋል።
በተያዘው የምርት ዘመን 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡም አንስተዋል። የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከደላላ የፀዳ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ኢንዲስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የክልሉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አሠራርን በማዘመን ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል እንደሚገባም ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች 70 በመቶ ማምረት እንዲችሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ውይይቱ ውጤታማ የሚኾነው የአርሶ አደሮችን፣ የኢንዱስትሪዎችን እና የገበያ አቅርቦትን ችግር መፍታት ሲቻል ነው ብለዋል።
የ”ኤምኤስኤ” ኤክስፐርት እና የማኑፋክቸሪንግ ብዝነስ ግሩብ የባሕርዳር ቅርጫፍ አስተባባሪ አበረ አበራ ባለፈው ዓመት ከ50ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን አንስተዋል። ከ200ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ነው የጠቆሙት።
የመርከብ ዩንየን ሥራ አሥኪያጅ ጌታቸው እሸቱ ክልሉ ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ምቹ እና ምርታማ መኾኑን ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት አኩሪ አተር እና ቦለቄ ለመላክ ከአርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው ብለዋል።
ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩም የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

