በአብክመ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚሰጣቸው አገልግሎቶች/ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት/ አላማዎች
የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተቋቋመበት ደንብ ቁጥር 143/2008 ዓ.ም መሠረት የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፡፡
አላማ አንድ
- ዘመናዊ የቅድመ ምርትና ድህረ ምርት ቴክኖሎጅና የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከትና ለክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግብዓትነት የግብርና ምርት ውጤቶች መጠን፣ጥራትና ምርታማነት ከፍ እንዲል በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፤
አላማ ሁለት
- በተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣በምርት ማሰባሰቢያ እና በገጠር ሽግግር ማዕከላት እንዲሁም በተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ተፈላጊው ቅንጅት እንዲፈጠር በማድረግ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ማፋጠን ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 143/2008 ዓ.ም መሠረት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡
- የተቀናጀ አግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የገጠር ሽግግር ማዕከላት፣ የአነስተኛና መካከለኛ ክላስተሮች ሸዶች፣ህንጻዎችና ሸዶች እንዲሁም የምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላት እንዲገነቡ ያደርጋል፤ ያስተዳድራል፤ ያከራያል በሊዝ ወይም በሽያጭ ያስተላልፋል፤ ከቦርዱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የስራ አመራር ተግባሩን በውል ለሌሎች አካላት ያስተላልፋል፡፡
- በክልሉ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያለማል፤ያስተዳድራል፤ ለአልሚዎች በሽያጭ ወይም በኪራይ መልክ ያስተላልፋል፡፡
- የተቀናጀ አግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የገጠር ሽግግር ማዕከላትን፣ የአነስተኛና መካከለኛ ክላስተሮችን፣ ህንጻዎችና ሸዶችን እንዲሁም የምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላትን ጠቀሜታ ያስተዋውቃል፤ የግል ባለሃብቶችን የሚስቡ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ ይፈፅማል፤
- ፍላጎቱ ካላቸው የግል ባለሃብቶች ጋር በመስማማት በጋራ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ይሰማራል፤
- በተቀናጁ የአግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በገጠር ሽግግር ማዕከላትም ሆነ በምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላት መካከል እንዲሁም በተቀናጁ አግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲፈጠር ያበረታታል፤
- የተቀናጀ የአግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣የሸዶችንና የክላስተር ማዕከላትን መሰረተ ልማት አውታሮች ጥገና፣ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስራዎች ይመራል፤ የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲኖር አስፈላጊውን ይፈጽማል፤
- ከፓርኮች ጋር በተያያዘ ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔዎችን ያፈላልጋል፤ ከአቅሙ በላይ ሆነው የተገኙትን ደግሞ በሕግ አግባብ መፍትሔ እንዲያገኙ አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል፤
- የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ በህግ መሰረት ውሎችን ይዋዋላል፤ በስሙ ይከሳል ይከሰሳል፤
- ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ያከናውናል፤